Tuesday, September 2, 2008

The EPRDF Strategy to bring prosperity in 25 years

Home Sections Forums Reporter - English Ver. Register Contact Us
Member Area Wednesday Sep 03rdHome Sections የኢሕአዴግ ሃሳብና - ጉባዔው
የኢሕአዴግ ሃሳብና - ጉባዔው
Sunday, 31 August 2008
በጌታቸው ንጋቱ

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔውን በመስከረም 2ዐዐ1 መጀመሪያ ላይ ያካሂዳል፡፡ ፓርቲው፣ በጉባዔው ላይ የሚያቀርበውን ረቂቅ የፓርቲው አመራሮች ካዩት በኋላ ማሻሻያዎች ካሉ ታክለውበት ለጉባዔው ይቀርባል፡፡

7ተኛው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ..ስኬታማ ተግባሮቻችንን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ሕዳሴ በፅኑ መሠረት ላይ እንገነባለን.. በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን በተለያዩ መስኮች ፓርቲው ያካሄዳቸው እንቅስቃሴዎችም በተዘጋጀው ሪፖርት ውስጥ ተካተዋል፡፡ 7ተኛው ድርጅታዊ ጉባዔም የሚወያይበት ዋነኛ አጀንዳ በኢሕአዴግ ምክር ቤት የቀረበው ይኸው ሪፖርት ነው፡፡ ሪፖርቱ በፖለቲካና ድርጅታዊ ጉዳዮች በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም በውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደህንነት ዙሪያ የተጠናቀረ ነው፡፡

..ተሃድሷችን ፍሬ ማፍራት ጀምሯል.. ሲል የሚጀምረው ሪፖርት ድርጅቱ የቆመለትን አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ኘሮግራም በተግባር ላይ ለማዋል ላለፉት 17 ዓመታት በስልጣን ላይ ሆኖ ሲታገል መቆየቱን ይገልፃል፡፡ ከነዚህ ውስጥም በመጀመሪያዎቹ 11 ዓመታት በርካታ ጥያቄዎችን በጥራት አለመመለሳቸውንና ብዙ መሥራት እየተቻለ በግልፅነት እጦት ወደ መቆም ከማምራቱም በላይ በተለይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ማሽቆልቆል አምርቶ እንደነበር ይገልፃል፡፡

በዚሁ የሪፖርቱ መግቢያ ላይ ኢሕአዴግ አገሪቱን በፈጣን እድገትና በተሟላ የዴሞክራሲ አቅጣጫ ማራመድ መጀመሩን ሲገልፅ ..የተያያዝነው የለውጥ ጉዞ በየደረጃው የሚያጋጥሙትን ችግሮችና ፈተናዎች በብስለት እየፈታን በጀመረበት ፍጥነት እንዲቀጥል ለማድረግ ከቻልን መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አገሮች ጐራ ካሰብነው ወቅት ጥቂት ቀደም ብለን ልንቀላቀል እንደምንችል በእርግጠኝነት መናገር የምንችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው.. ይላል፡፡

ከተሃድሶው በኋላ ሚሊዮኖች የኢሕአዴግን ሰልፍ ተቀላቅለው አባላት መሆናቸውን የሚያመለክተው ሪፖርቱ፣ ..በዚህ መሠረት በአሁኑ ጊዜ ድርጅታችን በአገር አቀፍ ደረጃ 4.5 ሚሊዮን ያህል አባላት ያሉት ድርጅት ሆኗል.. ይላል፡፡ ድርጅቱም በከተሞች ያሉትን ሳይጨምር በገጠር ብቻ ከ3.7 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና የገጠር ሙያተኛ አባላት ለማቀፍ መቻሉንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ድርጅቱ በገጠር ቀበሌዎች ያለው ህልውናም በነዚሁ ..ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች.. ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያመለክታል፡፡

አባላቱን በዚህ የትግል ሂደት የሚመራ ራሱን እያበቃ ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች የሚሠማራ የብቁ የሠው ኃይል ፍላጐት ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል የመካከለኛ አመራር ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡ ተከታታይ ስልጠናዎች በመስጠት በ1999 ዓ.ም. ከህዳር እስከ የካቲት በሁለት ዙር 15..354 የከፍተኛና መካከለኛ አመራር፣ በ2ዐዐዐ ዓ.ም. ክረምት ለ16..ዐዐዐ የመካከለኛ አመራር አባላት ስልጠና መሠጠቱንና እየተሰጠም መሆኑን ያመለክታል፡፡

የቀበሌ አመራሮችንም አቅም ለመገንባት ሁለት ተከታታይ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን በድምሩ 46ዐ..ዐዐዐ ያህል የቀበሌ አመራር አባላት መሠልጠናቸው ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የትምህርት ደረጃ የሚያሟሉና በተግባር እየተፈተኑ ብቃታቸውን በማረጋገጥ ላይ የሚገኙ በየወረዳው ከ25-30 የሚደርሱ በድምሩ 15 ሺ ያህል የመካከለኛ አመራር ካድሬዎች መመደብ መቻሉንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ኢህአዴግ ሁሉም አባላቱ በመሠረታዊ ድርጅቶችና ከዚያም አልፎ በጥናት ህዋሳት እንዲዋቀሩ መደረጉን ሲገልፅ 4.5 ሚሊዮን አባላቱ በ18..263 ያህል መሠረታዊ ድርጅቶችና በ238..380 ያህል የጥናት ህዋሳት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱበት የጥንካሬ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሪፖርቱ ያስቀምጣል፡፡

በገጠር አካባቢዎች ሴቶችና ወጣቶችን በተመለከተ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ሪፖርቱ ሲገልፅ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ የሚያረጋግጡ ፓኬጆች መዘጋጀታቸውን፣ ፓኬጆቹ ከተዘጋጁ በኋላ በተወሰነ ደረጃ ወደ ተግባር መሸጋገር የተቻለ መሆኑንና አሁን ደግሞ ወጣት እና ሴት አባላቶች በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመራር ስር የወጣቶችንና የሴቶችን ትግል ለመምራት አስበው በቀረጿቸው የየራሳቸው ኘሮግራሞች የኢህአዴግን ትግል ወደ ከፍተኛ ትግል እንደሚያሸጋግሩ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

በገጠር አካባቢዎች የሰራቸውን ሥራዎች ፓርቲው ሲዘረዝር ..በገጠር ለኪራይ ሰብሳቢነት አመቺ የነበረው የፖለቲካ ኢኮኖሚ እየተናደ ለልማታዊነትና ዴሞክራሲያዊነት እንዲሁም በእነዚህ ላይ ለተመሠረተ መልካም አስተዳደር የተመቸ ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል.. ይላል፡፡ አርሶ አደሩ በተቻለው አቅም የፖለቲካ ተሳትፎ ቢያደርግም በቂ ትምህርትና ልምድ ስለሌለው ሥልጠና እንደሚያስፈልገው ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡ በገጠር መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እጅግ ተፈላጊ የሆነው የሕዝብን የተደራጀ ተሳትፎ የማረጋገጥ ጉዳይ ይበልጥ እየቀለለና እየተሳካ የሚሄድበት ሁኔታ መፈጠሩንም ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡

በገጠር ያለውን የኢሕአዴግ እንቅስቃሴ በሠፊው የቃኘው ይኸው ሪፖርት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በገጠር ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ለማጐልበት የሚከተላቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡ በቅድሚያ ከዚህ ቀደም የተዘጋጁትን የመልካም አስተዳደር ፓኬጅና የሲቪል ሠርቪስ ማሻሻያ ኘሮግራሞችን ያዋሃደ አንድ ወጥ ኘሮግራም እንደሚቀረፅ፣ በገጠር የሕዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የተቋቋሙ የሕዝብ አደረጃጀቶችን ማስፋትና ማጠናከር እንደሚሠራና በገጠር የትምህርትና የባህል ደረጃ ዝቅተኛነት ትምህርት በማስፋፋትና የሕዝቡን የባህል ደረጃ ከፍ የማድረግ ስልቶች እንደሚጠቀም ያመላክታል፡፡

ኢሕአዴግ በከተማ ያለውን የፖለቲካና ድርጅታዊ ተግባራት አፈፃፀም እና የሚገኝበትን ሁኔታና ቀጣይ ተግባራት አስመልክቶም በአሁኑ ሠዓት በድምሩ ከ7 መቶ ሺህ በላይ የሚቆጠሩ አባላት በከተሞች እንዳሉት ሲገልፅ አባላቱም በሴቶች፣ በወጣቶችና በሌሎችም ማህበራት ውስጥ በመግባት ህብረተሰቡን ለልማትና ለዴሞክራሲ ማታገል መጀመራቸውን ያስረዳል፡፡ ..እጅግ የሚበዛው የከተማ ሕዝብ ኑሮው ከአነስተኛና ጥቃቅን ተቋሞች ላይ ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወቱ ግለሰቦችን በአባልነት ለመመልመልና ለማሰልጠን ጥረት ተደርጓል.. የሚለው ሪፖርቱ ለከተሞች በተቀየሱ የትግል አጀንዳዎች ዙሪያ የአባላትን ብቃት ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልፃል፡፡

..የከተማው የልማት እንቅስቃሴ ዛሬም ቢሆን መድረስ የሚገባው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ ይህም በመሆኑ እንደገጠሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግንባር ቀደም የልማት አርበኞች ማፍራት ሳይቻል ቀርቷል.. የሚለው የ7ተኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ረቂቅ ሪፖርት በአባልነት የታቀፉት ግንባር ቀደሞች የዘርፉ ተዋናይ መሆን ያልቻሉና አቅም ያልፈጠሩ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡

ኢሕአዴግ በገጠር ያሉት 3.7 ሚሊዮን አባላት ቁጥር ለጊዜው እንደሚበቁትና ዋነኛው ስራ የአባላቱን አቅም ማጠናከር መሆኑን ሲገልፅ በከተማ ግን በሠፊው አባላት መመልመልና የማስፋት ሥራ እንደሚሰራ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

በከተሞች የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲን መሠረት ለማስፋት የሚካሄደው የኪራይ ሠብሳቢነት መሠረትና ምንጭ የሆኑትን ችግሮች ማስወገድ ሲቻል መሆኑን የሚያትተው ሪፖርቱ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማትን እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ድጋፍ ተቋማትን ለማጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ ያብራራል፡፡

በሪፖርቱ የግሉ ሚዲያ የሚገኝበት ሁኔታም የተዳሰሰ ሲሆን ..የግሉ ሚዲያ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ገንቢ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ በህትመትና በኤሌክትሮኒክ ዘርፍ የተጀመረው ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ጥረት ተደርጓል.. በማለት የሚገልፀው ሪፖርቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የግል ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በኤፍ.ኤም የስርጭት መስመሮች መከፈቱን ያመለክታል፡፡

..ከምርጫ 97 በፊትና በኋላ በግል የሕትመት ሚዲያው አካባቢ የታየውን በጐ ያልሆነ አዝማሚያ መልክ ለማስያዝ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱንና ሕግን አክብረው ባልተንቀሳቀሱ ሚዲያዎች ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል.. የሚለው ይህ ሪፖርት ከፊት ይታይ የነበረውን ..አፍራሽ አዝማሚያ.. በተወሰነ ደረጃ ማርገብ መቻሉን ያትታል፡፡ መንግሥትም ለግሉ ሚዲያ በተሻለ ደረጃ በእጁ ያሉትን መረጃ እንዲያገኝ ማድረጉን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

..ይህም ሆኖ በሚዲያ አካባቢ የሚንፀባረቀው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር እንደገና በማገርሸት በከፋ መልኩ መገለፅ ጀምሯል፡፡ ይህን ችግር መገንዘብና ቀደም ሲል አፍራሽ አዝማሚያ የነበረው ኃይል በሚዲያው ላይ የበላይነት ይዞ የነበረበት ሁኔታ እንዳይመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል.. በማለት መንግሥት ሚዲያው ለዴሞክራሲና ልማት መጠናከር በሚበጅ አኳኋን እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ አስፈላጊውን ፖለቲካዊና ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉ ተገቢ መሆኑ ይገልፃል፡፡

በዚሁ የሪፖርቱ ክፍል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጐላ ብሎ የሚታይ የሚና መደበላለቅ ችግር የሚታይባቸው በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል ድርጅቶቹ ከባህሪያቸውና ከተልዕኳቸው በመነሳት የሚተዳደሩበት ራሱን የቻለ ሕግ እንዲወጣና በቀጣዩ ዓመትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅና በተግባር ላይ እንደሚውል አስታውቋል፡፡

የሪፖርቱ የመጀመሪያ ክፍል ሲጠቃለልም ..የፖለቲካ ፅንፈኝነትና ጤናማና የተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ለመገንባት የሚጫወተውን አሉታዊ ሚና መገንዘብ በሚቀጥሉት ዓመታት ገንቢ የተቃዋሚነት ሚና መጫወት ከጀመሩ ፓርቲዎች ጋር ከሚናቸው ጋር የሚመጥን ግንኙነት ኢሕአዴግ እንደሚኖረው ይገልፃል፡፡ ገንቢ ሚና የሚጫወቱትን ፓርቲዎች ኢሕአዴግ እንደሚያበረታታና ሕገ ወጦችን ተከታትሎ ለሕግ ማቅረብ እንደሚያስፈልግም አመልክቷል፡፡ ..ከሁለቱ መካከል የሚወላውለትን ደግሞ ሚናቸውን እንዲለዩ ለማድረግ በመጣር የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ በይበልጥ ጤናማ አቅጣጫ ተከትሎ እንዲያድግ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል.. ይላል፡፡

በሪፖርቱ ክፍል ሁለት የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ተግባራት የተዳሰሱ ሲሆን በ1996 ዓ.ም. 10.37 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የነበረው አጠቃላይ ምርት በ2ዐዐዐ ዓ.ም. ወደ 16.45 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማደጉን ያመለክታል፡፡ በፊት በሄክታር ይመረት ከነበረው 11.9 ኩንታል ምርት በሄክታር ወደ 17 ኩንታል ከፍ ማለቱንም ያመለክታል፡፡

ኢሕእዴግ ለወጣቶችና ለሴቶች ትኩረት እንደሚሰጥ በተለያዩ የሪፖርቱ ክፍሎች ላይ የተመለከተ ሲሆን ..የገጠር ወጣቶች በገጠር መሬት ላይ ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ ሆነዋል ማለት አይቻልም፡፡ ሴቶችም በሁሉም አካባቢዎች በዋነኛነት በቤት ሥራ በመጠመዳቸው፣ በወንድ ትምክህተኝነት አስተሳሰብ ተፅእኖ ሥር በመውደቃቸው በበርካታ አካባቢዎችም የመሬትና የንብረት ባለቤት ያለመሆን ችግር ስላለባቸው ከሂደቱ እኩል ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቀርተዋል.. ይላል፡፡

በመሠረተ ልማት መስክ 15 ሺህ ቀበሌዎች የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን፣ ከአገሪቱ ቀበሌዎች ግማሽ ያህሉ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ እና ሌሎችም ሲዘረዝሩ አብዛኛው ስኬት ከኢሕአዴግ 6ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ውሣኔዎች በኋላ የተገኙ ስኬቶች መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

የትምህርትና ጤና ሽፋን በሪፖርቱ ሰፊ ዳሰሳ የተደረገባቸው ሲሆን በአገሪቱ በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን 13 ዩኒቨርሲቲዎች ጨምሮ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር 21 መድረሱን ያመለክታል፡፡ ..በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ቢያንስ 1ዐ ተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችን የመገንባት ስራ ለመጀመር ጥናት እየተካሄደ ነው.. የሚለው ሪፖርት ዩኒቨርሲቲዎች የሚቀበሏቸው ተማሪዎች በፊት በተቀመጠው 7ዐ በመቶ በሳይንስና ቴክኖሎጂ (40 በመቶ የሚሆኑት የተለያዩ የምህንድስና ዘርፎች፣ 3ዐ በመቶ የሚሆኑት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች) እንደሚሰለጥኑ ያመለክታል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ካሪኩለም መሻሻል፣ የውጭ ባለሙያዎችንና ዩኒቨርሲቲዎች ከአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ማቀራረብ ትኩረት እንደሚሰጠውም ተመልክቷል፡፡

ሪፖርቱ በውጭ ግንኙነት፣ በማይክሮ ፋይናንስ፣ በኢንቨስትመንት የተገኙ ለውጦችንም አቅርቧል፡፡ ስለ ወቅታዊው የኢትዮ-ሶማሊያ፣ ኢትዮ-ኤርትራ ጉዳዮችም ሪፖርቱ የገለፀ ሲሆን ስለቀጣይ የውጭ ግንኙነት ተግባራትም አመላክቷል፡፡

ኢሕእዴግ በዚህ የ7ተኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ገቢውንና ወጪውን ሪፖርት የሚያደርግ ሲሆን በ1999 ዓ.ም. ብር 17.8 ሚሊዮን እንዲሁም በ2000 ዓ.ም. 11.4 ሚሊዮን ብር በድምሩ 29.2 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን ሲገልፅ የ1999ኙ ገቢ 7ዐ በመቶ ያህሉ የተገኘው አባል ድርጅቶች ካደረጉት የገንዘብ አስተዋፅኦ ሲሆን ቀሪው በባንክ ተቀማጭ ከሆነ ገንዘብ የተገኘ ወለድና የመሳሰሉት ገቢዎች የተገኙ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ከነዚህ ገቢዎች በተጨማሪ በ2ዐዐዐ ዓ.ም. ብሔራዊ ድርጅቶችና ኢሕአዴግ በጋራ ከየክልሉ ሕዝብ ድርጅቱን ለማጠናከሪያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ባካሄዱት ጥረት እስካሁን 75.6 ሚሊዮን ብር መሠብሰቡን ሲገልፅ በስምምነቱ መሠረት የገቢው 3ዐ በመቶ ለክልሎች እንደሚሰጥ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም ኢሕአዴግ በራሱ ከግል ባለሃብቶች የማሰልጠኛ ማዕከሉን ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ለማሰባሰብ ባካሄደው እንቅስቃሴ በዓይነትና በብር 7ዐ ሚሊዮን ያህል ገቢ አግኝቷል፡፡ በአጠቃላይ ኢሕአዴግ በዚህ ዓመት ብቻ 167 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን ከሪፖርቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፓርቲው የፖለቲካና ድርጅታዊ ስራዎቹን ለማከናወንም በ1999 ዓ.ም. 18.8 ሚሊዮን ብር ሲያወጣ በ2000 ዓ.ም. 18.7 ሚሊዮን ብር በድምሩ 37.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ሪፖርቱ በማጠቃለያው ..የተሃድሶውን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል በከፍተኛ ደረጃ የተቀናጀ ድርጅታዊና መንግሥታዊ አመራርና ሠፊ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተሃድሷችንን ፍሬ ለአዳዲስ የተሃድሶ ድሎች እንጠቀምበት.. ይላል፡፡
Next >

[
Copyright © 2008 Reporter - Amharic Version. Designed by isynconline.com

No comments: