Friday, September 5, 2008

Rent Seeking or Productivity Seeking Behavior? What is the Difference and who is the judge? The Ethiopian experience

Saturday Sep 06thHome Sections ‘የኪራይ ሰብሳቢነት’ ፖለቲካ በኢህአዴግ ቅኝት
‘የኪራይ ሰብሳቢነት’ ፖለቲካ በኢህአዴግ ቅኝት
Friday, 29 August 2008
በየማነ ናግሽ


የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ህልውና ከሚያረጋግጡ ዋነኛ ምሰሶች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማለት በአንድ አገር የተለያዩ አቋም፣ ፕሮግራምና ርዕዮተ ዓለም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ፕሮግራማቸውና አመለካከታቸው በህብረተሰቡ ለማስረፅ በነፃነትና በእኩልነት የሚንቀሳቀስበት መድረክ መኖርም ያስፈልጋል፡፡


በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እየጎለበተ ወይስ እየጠፋ ነው? አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስርዓትና የመድብለ ፓርቲን ስርዓት ይጣጣማሉ ወይስ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ? የሚለውን በዚህ ፅሑፉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይዳሰሳሉ፡፡

ኢትዮጵያን ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የሚከተለው “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ” ርዕዮተ ዓለም ከፓርቲው አባላትና መሪዎች አልፎ በሕዝቡና በምሁራን የዘለቀ እንዳልሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶቹም፤ የርዕዮተዓለሙ መሠረታዊ ፍልስፍና “ሶሻሊዝም” እንደሆነ ሲተቹ ሌሎችም፣ በኢትዮጵያ ምድር ብቻ የተፈጠረ አዲስና ያልተሞከረ ፅንሰ ሃሳብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ግን ርዕዮተ ዓለሙ በኢትዮጵያ አማራጭ የሌለውና የራሱ ፍልስፍናዊ መሠረት ያለው እንደሆነ ይናገራል፡፡

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርእየተ ዓለም አመጣጥና መሠረት ራሱን የቻለ ጉዳይ ሆኖ ራሱ ገዢው ፓርቲ ከሚሰጠው ትርጓሜና መርህ አንፃር ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ካለውና ራሱ ገዢው ፓርቲም የሚያምንበት “መድብለ ስርዓት” ጋር ያለውን ግንኙነት ምን ይመስላል? በሚል መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡

ኢህአዴግ በቅርቡ አባላቱን ርዕዮተ ዓለሙን በማስረፅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በሚሰጣቸው ስልጠናዎች በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከፀደቁት ሰነዶች መካከል “የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግልና አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ውስጥ ስለ አገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ በተለይ በሰነዱ ውስጥ ገዢው ፅንሰ ሃሳብ ሆኖ የሚጠቀሰውና የአገሪቱ የፖለቲካ ትንታኔ ማዕከል ሆኖ ያገለገለው “የኪራይ ሰብሳቢነት” ፖለቲካ ነው፡፡

ልማታዊ መንግሥት መፍጠር ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊ የገቢ ክፍፍል ማምጣት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ እንደሆነ የሚያትተው ይህ ፅሑፍ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገልና አብዮታዊ ዴሞክራሲን ሊሸከም የሚችል ቅድመ ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል፡፡

“ቅድመ ሁኔታ ባልተሟላበት አገር ዴሞክራሲን ለመገንባት መሞከር በምድረ በዳ ዘር ከመዝራት የተለየ ውጤት አይኖረውም” በማለት ስርዓቱን ለመገንባት ሞክረው ተንኮታኩተው የወደቁ አገሮችን ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡

ለዚህም የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችና አስተሳሳቦች የበላይነት ለማጥፋት በልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ መተካት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነና ፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደሚያስፈልግ ያትታል፡፡

“የኪራይ ሰብሳቢነት ለማክሰም የሚደረገው ትግል የሚሳካው በቂ የዴሞክራሲ መድረክ ሲኖር ነው” የሚለው ይህ ሰነድ፣ ሁለቱ ተፃራሪ አመለካከቶች በግልፅ ወደ መድረክ ቀርበው መሻኮት ሲችሉ፣ ልማታዊ አስተሳሰብ ነጥሮ በመውጣት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን ያሸንፋል የሚል አቋም ታክሎበታል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች መታፈን እንደሌለባቸው የሚተነትነው ይህው የገዢው ፓርቲ አቋም፣ በሕዝቡ ጭንቅላት ውስጥ የሰፈሩ በመሆናቸው ዴሞክራሲ ኪራይ ሰብሳቢነትን ረለመናድሪ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን አበክሮ ይገልፃል፡፡

ዴሞክራሲን ለመዝራት፣ በቅድመ ሁኔታዎች ከተጠቀሱ መካከል የኪራይ ሰብሳቢነት ስርዓት መናድ፣ ሕዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ትምህርትና ስልጠና ማስፋፋት፣ አርሶ አደሩ የስርዓቱ ዋነኛ ተዋናይ ማድረግ ወዘተ ይገኙባቸዋል፡፡ የእነዚህ ሰፋፊ ተግባራት ግቦች ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ዴሞክራሲያዊ ባህልና ዜጋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት መፍጠር ነው፡፡

በዚሁ ጉዳይ ትልቅ ትንተና ከተሰጣቸው መካከል “የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲ” ሲሆን፣ “የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት በፍፁም የማይተካ ሚና አላቸው” ይላል፡፡ በመሆኑም “ፓርቲዎች በህግ መሠረት እንዲደራጁ፣ ህግና ስርዓት አክብረው ስራቸውን በነፃነት እንዲያካሂዱና ረየሕዝብ ድጋፍ እንዲያገኙሪ” ቢፈቀድም ፣እንደየባህሪያቸው የሚጫወቱትን ሚና፣ የመቆጣጠርን አስፈላጊነት ተሰምሮበታል፡፡

“አብዮታዊ ዴሞክራሲ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው” በማለት፣ ኪራይ ስብሰባነት ተንዶ፣ ክብደት በማይሰጥበት ወቅት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ያላቸው ከአንድ በላይ ፓርቲዎች ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል፡፡ “". ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የትጥቅ ትግልንም በሚጨምር አኳኋን ከባድ ፍልሚያ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ድርጅቶች አንድም ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ካምፕ እየተጠቃለሉ፣ አልያም ጠቅልለው ኪራይ ሰብሳቢነት እየገቡ መሄዳቸው አይቀርም” በማለት ከፍልሚያው ከባድነት ‘ሃይሎች መሸጋሸጋቸው አይቀሬ ነው’፣ “ከአጭር ጊዜ አኳያ ያለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ኢህአዴግ ብቻ” እንደሆነ ይተነትናል፡፡

ኢህአዴግን በዚሁ አቋሙን ያንፀባረቀበት ሰነድ፣ ከራሱና፣ ከአጋር ድርጅቶቹ “ውጪ ያሉ ድርጅቶች በመሰረቱ በኪራይ ሰብሳቢነት ካምፕ ያሉ ናቸው” በማለት ይፈረጃቸዋል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎች አሁንም እንደ ምርጫ 97 ፍልሚያ ተሸጋሽገው ወደ አንድ የመምጣት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል በመገመት፣ “".የኪራይ ሰብሳቢነት የዜሮ ድምር ፖለቲካ በውስጣቸው የማይጠገን ልዩነት” መፈጠሩን ያትታል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት የዜሮ ድምር ፖለቲካ በውስጡ ለግጭት መነሻ የሚሆን መሰረታዊ ባህሪ እንዳለውና፣ “በኢትዮጵያ ኪራይ ሰብሳቢዎች በሰላማዊ ትግል ዙሪያ የተለያየ አቋም” እያራመዱ እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ኢህአዴግ፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች በሶስት ደረጃዎች ይከፋፍላቸዋል፡፡ ዋናዎቹ የጥገኝነት ሃይሎች “የትም ፍጪው፤ ዱቄቱን አምጪው” መርህ የሚከተሉ፣ ከማንኛውም የጥፋት ሃይሎች ጋር የሚሰሩና በአሁኑ ወቅት ለኤርትራ መንግሥት በጀሌነት የሚያገለግሉ፣ ፣ፀረ ሰላም ሃይሎች፣ ናቸው፡፡ ሌሎችም፣ ጠቅልለው ወደ ፀረ ሰላም ሃይሎች ካምፕ ያልገቡ፣ ነገር ግን ህገመንግሥቱን በመፃረር ለፀረ ሰላም ሃይሎች መከታና ከለላ የሚሆኑና ፣ወላዋይ አቋም፣ ያላቸው ናቸው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ፣ ኪራይ ሰብሳቢ አቋማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉ ላይ ከሞላ ጎደል እምነት ያላቸው ሊባሉ የሚችሉ በማለት ይፈርጃቸዋል፡፡

ኢህአዴግ ፣ኪራይ ሰብሳቢ፣ ተቃዋሚዎች አበክሮ እንደሚታገላቸው የገለፀ ሲሆን፣ የህገ መንግሥቱ ልዕልና ተቀብለው የኪራይ ሰብሳቢነት አላማቸውን በተመቻቸ ሁኔታ የሚያራምዱበት የተመቻቸ ሁኔታን መፍጠር ለአብዮታዊ ዴሞክራሲም ጠቀሜታ እንዳለው ይገልፃል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚያራምደው ኢህአዴግ፣ ፣ኪራይ ሰብሳቢዎቹ፣ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ሊያከስማቸው እንደሚፈልግ የተገለፀ ሲሆን፣ “የትግሉ ዋነኛ ግብ ፀረ-ሰላም ድርጅቶች ማክሰም ወይም ተገደው የሰላሙን መንገድ እንዲቀበሉ ማስገደድ” እንደሆነ ነው፡፡ “በሰላም ጉዳይ ላይ ወላዋይ አቋም ያላቸው ሃይሎች አንድም መወላወሉን ትተው ወደ ሰላም ካምፕ እንዲጠቃለሉ፣ አልያም ለይቶላቸው ፀረ-ሰላም እንዲሆኑ ማስገደድ አለብን” በማለት ገዢው ፓርቲ በተቃዋሚዎች ያለውን ፍረጃና የያዘውን የማጥፋት ዕቅድ ግልፅ አድርገዋል፡፡

ይህንን የኢህአዴግ ፍርጃ በተቃዋሚዎቹ በኩል ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሲሆን በመድለ ፓርቲ ስርዓት ላይ “ያንዣበበ አደጋ” አድርገው አይተውታል፡፡

የኢዴአፓ-መድኅን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ኢህአዴግ ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ህግ መውጣቱ አንድ ነገር ሆኖ፣ በተግባር እየታየ ያለው ተቃዋሚዎች ዓይነተኛ ፣የማክሰም፣ ሂደት ግን አስግቷቸዋል፡፡

“ይሄም የመነጨው ከዚሁ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ነው” ብለዋል፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መሰረቱ ዴሞክራሲ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ልደቱ፣ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ የሌሎች አስተሳሰቦች መቀበል የሚችል ርእዮትም አይደለም” ብለዋል፡፡

ሲጀመር “አብዮታዊ ብሎ ዴሞክራሲ የለም፡፡ ሁለቱም ተቃራኒ ናቸው” በማለት አብዮት ስር ነቀል ለውጥ፣ ዴሞክራሲ ግን በሂደትና ቀስ በቀስ የሚመጣ ስርዓት በመሆኑ ተቃራኒ አስተሳሰቦች “fallacy” እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ከዚህ የፀዳ አስተሳሰብ ቢኖረው ተቃዋሚዎች እንደ ጠላትና አገር አፍራሽ አድርጎ ማየቱን አቁሞ ገንቢ በሆነ መልኩ ቢያያቸው ነበር” ብለዋል፡፡

“ኢህአዴግ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም አሁን ካለው የዓለም ፖለቲካ አሰላለፍ፣ ከዕርዳታና ማግኘትና ከውጭ ግንኙነት የማያስኬድ ሆኖ ነው እንጂ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለአንድ መደብና ርዕዮተ ዓለም የሚታገል ስርዓት ነው” በማለት ርዕዮተ ዓለሙ የመድብለ ስርዓት ተቃራኒ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለካድሬዎች እየተሰጠ ያለው ይሄ ስልጠናም ከዚህ አንፃር አይተውታል፡፡

የህብረት ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ የአቶ ልደቱ ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ “ኢህአዴግ መድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚደግፍ ፀባይም የለውም”፡፡ ፕ/ር በየነ “አብዮታዊ ዴሞክራሲና መድብለ ፓርቲ ስርዓት ‘እሳትና ጭድ’ ናቸው አብረው የሚሄዱ አይደሉም” በማለት ኢህአዴግ እየሰጠው ያለው ከላይ የተገለፀው ስልጠና መስጠቱ “የሚገርመኝ አይደለም” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ለማስፈን ተስፋ ሳይቆርጡ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚናገሩት ፕ/ር በየነ፣ በተለይ በቅርቡ ከሌሎች አገሮች በጋራ በፈጠሩት “የምክክር መድረክ” አማካኝነት የተሻለ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

በኢህአዴግ ውስጥ ብቃት ያላቸው አመራሮች መኖራቸው የሚቀበሉ ፕ/ር በየነ፣ እነዚህ አመራሮች ጊዜያቸውን “ጨለምተኝነት አካሄድን ይዞ ብርሃን የማይታይበት ራእይ ይዞ ያ ሁሉ ሃብት ማባከን፣ የሰውን አእምሮ በእንደዚህ ዓይነት ከመበከል እንዲቆጠቡ” መክረዋል፡፡

የአገሪቱ ፖለቲካ እያጦዘው ያለው ህወሓት እንደሆነ የተናገሩት ፕ/ር በየነ፣ አንዳንድ የህወሓት ሰዎች “ከዚሁ ጨለምተኝነት” ወጥተው እነሱ ጋር እየሰሩ እንደሆነና የተቀሩት ከዚሁ የተሳሳተ መንገድ የሚወጡበትን ጊዜ በመመኘት፣ “መቼ እንደሚነቁ አላቅም” ብለዋል፡፡

የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ለልዓላዊነት ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፣ “ኢህአዴግ አጠቃላይ ህብረተሰቡን ለመቆጣጠር እየንቀሳቀሰ ነው” ብለዋል፡፡ የስልጠናዎቹን መንፈስ አስመልክተው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ የአገሪቱ የፖለቲካ መልከዓ ምድር ለማድረግ ነው” በማለት፣ ከዚህ የተለዩ አመለካከቶች ማጥፋት እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢ፣ ጠባቦች፣ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ወዘተ የሚሉ የኢህአዴግ ፍረጃዎች ፓርቲዎቹን ለማጥፋት እንደ “ቅድመ ማስጠንቀቂያ” አይተውታል፡፡

“በ97 ምርጫ የተደናገጠው ኢህአዴግ፣ መድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚፈልግ አይደለም” በማለት የአንድ ፓርቲ ስርዓት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡

Copyright © 2008 Reporter - Amharic Version. Designed by isynconline.com

No comments: